Wednesday, August 27, 2008

የፌዴራሊዝም ሰለባዎች

Reporter Thursday, 21 August 2008
በየማነ ናግሽ

በአንዳንድ አገራት ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ፌዴራሊዝም መከተል የምርጫ ጥያቄ ሳይሆን የግዴታ ሆኗል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ዓይነት ከሁለትና ከሦስት በላይ ብሔረሰቦች ያሉባቸው አገራት በቀድሞ ስርዓታት ጨቋኝና ተጨቋኝ፣ ገዢና ተገዢ፣ በዝባዥና ተበዝባዥ፣ የበላይና የበታች ሆኖ የቆየው ግንኙነታቸው እስከመተላለቅና መበታተን ሊያስከትል ይችላል፡፡ በመጨረሻ ችግሩ አንድ መፍትሔ ካልተበጀለት በስተቀር የአገር አንድነትና ህልውና እጅግ የሚፈታተን የፖለቲካ ቀውስ ይፈጠራል፡፡

በጉዳዩ ላይ ጥናት የሰሩ ምሁራን እንደሚሉት እንደዚህ ዓይነት ጤነኛ ያልሆነው ግንኙነት የነበራቸው ብሔር ብሔረሰቦች፣ ቡድኖች፣ ነገዶች ወይም ሃይማኖቶች የቆየ የተዛባ ግንኙነታቸውን በማስተካከል፣ በማቻቻልና በማስተዛዘን አብሮ የመኖርና የጋራ የወደፊት ዕድል ሊኖራቸው የሚችለው ብቸኛው መንገድ ፌዴራል ስርዓትን መጠቀም አማራጭ የለውም፡፡

ከላይ የተገለፁት ሁኔታዎች ማለትም የብሔረሰቦች ብዛት፣ የእርስ በርስ ግጭት፣ ሽኩቻ፣ ፉክክር የመሳሰሉ እሴቶች የኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ዋነኛ ግብዓቶች ናቸው፡፡ ያለፉት ስርዓታት እነዚህ ልዩነቶች አቻችሎ ለመሄድ ከመሞከር ይልቅ አንድነትን ለመፍጠር ሲባል አንድ ቋንቋ፣ አንድ ብሔር፣ አንድ ሃይማኖት የተከተለ አሃዳዊ ስርዓት ለመገንባት በተቃራኒው የሌሎችን ማንነትና ታሪክዊ እሴቶች ማጥፋት ፖሊሲ (Assimilation) ላይ ማተኮራቸውን ምሁራን ያስረዳሉ፡፡ ይህ የፈጠረው የፖለቲካ ቀውስና የብሔር ብሔረሰቦች የተበላሸ ግንኙነት ያስከተለው ችግር ስር የሰደደ በመሆኑ "ነበር" ተብሎ የሚወራበት ዘመን ቅርብ አይመስልም፡፡ አሁንም እርስ በርስ ትምክህተኛ፣ ነፍጠኛ፣ ተገንጣይ፣ ጎሰኛ፣ ዘረኛ፣ ቡድነኛ ወዘተ. የሚሉ ዋነኛ የቀውሱ መገለጫ አስፀያፊ ቃላት መጠቀም የተለመደ ነው፡፡

በ1983 ዓ.ም ስልጣን የተቆጣጠረው ኢህአዴግ ይህንን የቆየው የተዛባ ግንኙነት ሊፈውስ የሚችል ፌዴራሊዝም አበጀሁ ቢልም፣ ሁለቱ ስርዓት ተቃራኒ ወገኖች ማለትም "ጨቋኝና ተጨቋኝ" ከመለያየት ይልቅ ተቻችለው አንድ ላይ እንዲኖሩ የሚያስችል ስርዓት መሆኑን ተስማምተውበታል ማለት አይቻልም፡፡ በተጨማሪ አዲሱ ስርዓት ሁሉም የአገሪቱ የፖለቲካ ችግሮች መፍታት አልቻለም ብቻ ሳይሆን የራሱ የአፈፃፀም ችግሮች እየገጠሙት ይገኛል፡፡

ዶ/ር አሰፋ ፍሰሃ "Federalism Diversity and Regulation of Conflicts in the Horn" በሚል ጥናታዊ ፅሑፋቸው በአፍሪካ ቀንድ በተለይ ደግሞ በኢትዮጵያ የግጭትና አለመረጋጋት ዋነኛው መንስኤ ስልጣንና ሃብት በተወሰኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ቁጥጥር ስር ከመውደቁ ጋር የተያያዘ እንደሆነ በመግለፅ፣ ይሄው ያልተሳካ የአገር ግንባታ ኘሮጀክትና የአገር ተብለው የተለዩ ጠባብ እሴቶች ሌሎችን እንዲቀበሉዋቸው የማስገደድ ፖሊሲ፣ ብሔር ብሔረሰቦቹ ግንኙነታቸውን እንዳበላሸውና በጎሪጥ እንዲተያዩ ያደረገ መሆኑን በማስረዳት ለዚህ የመፍትሔ አማራጭ ሲሰጡ "ideally federalism appears to be the best conflict management device" በማለት የመጨረሻ አማራጭ እንደሆነ ይከራከራሉ፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም መልካም ፀጋዎኛና ተቃርኖዎቹ በተመለከተ ሰፊ ጥናት በማድረግና ሚዛናዊ የሆነ ግምገማ በማድረግ የስርዓቱ ጥንካሬዎችና ድክመቶች ለማብራራት የሚሞክሩት እኚህ ምሁር፣ የስርዓቱ አንድ ፈተና የሚሉት ስርዓቱ የዜጎች ህገመንግሥታዊ ሰብዓዊ መብታቸው እንዲከበር ወይስ እንዲጣስ እያደረገ ነው? በሚል በተለይ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በፈለገው ቦታ የመንቀሳቀስና የመሥራት (አንቀፅ 32) ሰብዓዊ መብትና ነፃነት በአንዳንድ ክልሎች እየተጣሰ መሆኑን በጥናታቸው አሳይተዋል፡፡

ህገመንግሥቱ ዕውቅና ለሰጣቸው 9 ክልሎች የተካለሉ በብሔር/ቋንቋ ቢሆንም በውስጣቸው የሚኖሩ ንዑስ ቁጥር የሚያዙ ዜጎች ችግር ትኩረት አለማግኘታቸው ይናገራሉ፡፡ በኦሮምያ፣ በቤንሻንጉል ጉምዝና በጋምቤላ ይህንን ችግር ገኖ ይታያል፡፡ እንዴት?

ኢትዮጵያ ውስጥ የብዙኃን ብሔር አለ?

እንደ ዶ/ር አሰፋ ጥናት በኢትዮጵያ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ብዙኃንና ንዑሳን (Majority and minority) ብሔረሰብ የሚል አገላለፅ አወዛጋቢ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ደረጃ ውስጥ አንድ ብሔር ብዙኃን (majority) ያለው ቁጥር ተደርጎ የሚወሰድ በስህተትና እውነትን ያላገናዘበ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በእርግጥ በአገር ደረጃና በክልል ደረጃ ለያይተን ማየት እንዳለብን ይጠቁማሉ፡፡ በአገር ደረጃ ትልቅ ቁጥር ያለው ብሔረሰብ (majority) አለ የምንል ከሆነ ከ50 በመቶ በላይ ቁጥር ያለው ብሔረሰብ ሊኖር ይገባል ይላሉ፡፡ ምሁሩ ይህ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የሌለው ሐቅ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ትልቅ ቁጥር ያለው የኦሮሞ ብሔረሰብ እንኳ ብንወስድ ፣ማጆሪቲ፣ ሊሆን እንደማይችል ለማስረዳት ይሞክራሉ፡፡ እንደ ምሁሩ አገላለፅ፣ በኢትዮጵያ እንዲህ ዓይነት ትልቅ ቁጥር ያለውና ፖለቲካውን በበላይነት የተቆጣጠረ ብሔረሰብ ባለመኖሩ የመንግሥት አለመረጋጋት፣ የጎሳ ግጭትና ስልጣን በብቸኝነት ለመቆጣጠር የእርስ በርስ ፉክክር አስከትሏል፡፡

ይህ በአገር ደረጃ ስንመለከተው እንጂ በክልሎች ግን አንድ ትልቅ ቁጥር ያለው ብሔረሰብና ሌሎች ንዑሳን መኖራቸው እሙን ነው፡፡ በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ትግራይ፣ አፋርና ሶማሊ ክልሎች በቁጥርም ሆነ በፖለቲካ የበላይ ሆኖ የሚቆጣጠር አንድ ብሔረሰብ ይኖራል፡፡

እነዚህ በትውልድ ክልላቸው ትልቅ ቁጥር (Majority) የሚወክሉ ብሔረሰብ ተወላጆች ግን በሆነ ምክንያት በሌሎች ክልሎች በሚገኙበት ጊዜ ንዑሳን ይሆናሉ፡፡ ስለዚህ እንደ አጥኚው ምልከታ በኢትዮጵያ ፣ብዙኃ ቁጥር፣ (Majority) እንደ ሁኔታው በየጊዜው ሊለወጥ የሚችል ነው፡፡

በአንዳንድ ክልሎች የስርዓቱ ተቃርኖ

በአምስቱ ክልሎች (ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ትግራይ፣ አፋርና ሶማሊ) አንድ የበላይ ቁጥር ያለው ብሔረሰብ እናገኛለን፡፡ የክልሉ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በበላይነት የሚቆጣጠረውም ይሄው አካል ነው፡፡ ወደ ሐረር፣ ጋምቤላና ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች በምንሄድበት ጊዜ ሁኔታው የተገላቢጦሽ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

በእነዚህ ክልሎች የበለጠ ቁጥር ያለው ብሔረሰብ በፖለቲካ ተሳትፎው አናሳ ነው፡፡ በሐረር ክልል በፖለቲካ ተሳትፎ የላቀ ተፅዕኖ ያላቸውና ቁልፍ ሚና እየተጫወቱ ያሉት የክልሉ ሰባት በመቶ ብቻ የሚሸፍኑ ሐረሪዎች እንደሆኑ ምሁራኑ (አጥኚዎች) ያስረዳሉ፡፡ በተመሳሳይ፣ በጋምቤላም በብዛት አንፃር የኑውሮ ብሔረሰብ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ቢሆንም፣ ተቀናቃኞቻቸው የሆኑት አኝዋክ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ የክልሉ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በበላይነት ይመሩታል፡፡ በቤንሻንጉል ጉምዝ ያለውም ከዚህ ብዙም የሚለይ አይደለም፡፡ በርታ የተባለ ብሔረሰብ ከፍ ያለ ቁጥር ያለው ቢሆንም የክልሉ ፖለቲካ የተቆጣጠረው የጉሙዝ ብሔረሰብ ነው፡፡ ደረጀ ፈይሳና ዶ/ር አሰፋ ፍስሃ በአካባቢው በሰሩት ጥናታዊ ፅሑፎች መሠረት በእነዚህ ሶስት ሁኔታዎች ብዙኃኑና አናሳ ብሔረሰብ የቁጥርና የፖለቲካ ስልጣን ለየቅል ናቸው፡፡

ዶ/ር አሰፋ እንደሚሉት በእነዚህ ክልሎች ያሉትን ፖለቲካውን በበላይነት የተቆጣጠሩት አናሳ ብሔሮች ራሳቸውን አድርገው ይቆጥራሉ፡፡

የስርዓቱ ሰለባዎች፣ አናሳ ብሔሮች

ዶ/ር አሰፋ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፁት፣ የአማራና የትግራይ ክልላዊ ህገመንግሥቶች ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የሆነ በትግራይ (አማራ) ክልል የሚኖር ዜጋ የክልሉን ተወላጆች የሚያገኙት ሁሉም ሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቶች ያጎናፅፋል፡፡ ሆኖም የኦሮሚያ ክልል ህገመንግሥት ስንመለከት "የኦሮሞ ሕዝቦች" ከማለት ውጪ በክልሉ ስለሚገኙ የሌላ ብሔረሰብ ተወላጆች (በተለይ ደገኞች) የሚለው ነገር የለም፡፡ በዚህ ምክንያት በርካታ ዜጎች በሥራና በፖለቲካ ተሳትፎአቸው የተገደቡ እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ በቋንቋና በሌሎች ምክንያቶች በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገዶች የስርዓቱ ሰለባዎች ሆነዋል፡፡ በኦሮምና በአማራ ብሔረሰቦች የሚከሰቱ ግጭቶች የችግሩ መገለጫዎች ናቸው፡፡

በተመሳሳይ በጋምቤላና በቤንሻንጉል ጉምዝ ህገመንግሥቶች በሁለቱም አንቀፅ 34 ላይ በአካባቢው የሚገኙ የሌላ ብሔረሰብ ተወላጆች መምረጥና መመረጥ እንደማይችሉ ይደነግጋል፡፡ እንደ ዶ/ር አሰፋ እይታ ይህ ከኢፌዲሪ ህገመንግሥት አንቀፅ 38 በነፃነት የመኖር፣ የመንቀሳቀስ፣ የመሥራት፣ ፖለቲካዊ ተሳትፎ ማድረግ መሰረታዊ ሰብዓዊ መብቶች የሚፃረር ነው፡፡

የጋምቤላ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳደር አቶ ጓነር በስልክ በሰጡን አስተያየት ግን፣ በክልሉ የሚገኙት የሌሎች ብሐረሰቦች ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ክልል ተወክለው እንዳሉና ተገለዋል የሚባለው ስህተት ነው በማለት አስተባብለዋል፡፡

በተለይ በቤንሻንጉል ጉምዝ በደርግ ጊዜ በሰፈራ ፕሮግራም ተገደው የተወሰዱ ደገኞች የክልሉ አጠቃላይ የሕዝብ ቁጥር 47 በመቶ የሚሸፍኑ ሆነው የከተማውን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በበላይነት የተቆጣጠሩ ቢሆንም ከክልሉ ፖለቲካዊ ተሳትፎ የተገለሉ እንደሆኑ የዶ/ር አሠፋ ጥናት ያሳያል፡፡

ይህ ችግር የኢትዮጵያ የፌዴራል ስርዓት በቋንቋ/በብሔር የተመሰረተ በመሆኑ የተነሳ አይደለም ወይ የሚል ጥያቄ ያቀረብንላቸው ዶ/ር አሰፋ፣ በቋንቋ የተመሰረተ ፌዴራሊዝም ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን እንደ ኢትዮጵያ ተመሳሳይነት ያላቸው አገሮች እንደ ህንድ፣ ስዊዘርላንድና ናይጄሪያ የመሳሰሉ የሚከተሉት ስርዓት እንደሆነና ስርዓቱ ጤነኛና መልካም ሆኖ እየሰራ ነው በማለት ተከራክረዋል፡፡ እንደ ዶ/ሩ ጥናትና ግንዛቤ፣ በኢትዮጵያ በተለይ በሶስቱም ክልሎች እየተከሰተ ያለው ግጭትና ተቃርኖዎች ከአተገባበርና ከአተረጓጎም ጋር የተያያዘ እንደሆነና አስቸኳይ የፖለቲካ መፍትሔ እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ፡፡

ግጭት ሲፈጠር የፀጥታ ሃይሎች በመላክ ግዚያዊ መፍትሔ ከማበጀት ይልቅ ለችግሩ ትኩረት በመስጠት የክልሎች ህገመንግሥት ከፌዴራል ህገመንግሥት ማጣጣምና ችግሩን መፍታት ይቻላል በማለት መንግሥታቱን ይወቅሳሉ፡፡ "ችግሩን ለመፍታት የሚጠይቀው ወጪ ከፍተኛ አይደለም፡፡ የፖለቲካ ፈቃደኝነት ብቻ ያስፈልጋል" የሚሉት ዶ/ር አሰፋ፣ "የራስ ዕድል በራስ የመወሰን መብት" ሲሰጥህ እዚያ ውስጥ ያሉትም ተመሳሳይ ዜግነታዊ መብት ያላቸው መሆን ማወቅ እንደሚያስፈልግና ስርዓቱ አላግባብ እየተተገበረ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ዶ/ር ሳራ ቫጋን በቤንሻንጉል አካባቢ ባደረጉት ጥናት ግጭቶቹ ሁለት ዓይነት መልክ ያስይዟቸዋል፡፡ አንደኛው በኙዌርና በአኝዋክ የእርስ በርስ የስልጣን ሽኩቻ ሲሆን፣ እነዚህ አንድ ላይ ከሌሎች (47 በመቶ የሚሸፍኑ) የብሔረሰብ ተወላጆች ጋር የሚያደርጉት ግጭት በሁለተኛ ደረጃ ይጠቅሳሉ፡፡ እነዚህ በተለይ በሰፈራ ፕሮግራም እዚያ ተገደው እንዲሰፍሩ የተደረጉት ደገኞች "ሁለተኛ ዜጎች" ሆነው እንደሚኖሩ ምሁራኑ በጥናታቸው አረጋግጠዋል፡፡

እነዚህ "ዜጎች ከፖለቲካዊ ተሳትፎ እንዲገለሉ ማድረግ በተዘዋዋሪ ውጡልን ማለት እንደሆነ"ና ይህ ደግሞ በፌዴራል ህገመንግሥቱ ምዕራፍ 3 ላይ የሰፈረው አጠቃላይ ሰብዓዊ መብቶች በሙሉ የሚፃረር እንደሆነ ዶ/ር አሰፋ አስረድተዋል፡፡ እንዲሁም ችግራቸው ለማስረዳት አቤት የሚሉበት ቦታም የላቸውም በማለት፣ በክልሎቹ እንባ ጠባቂ ተቋማት አለመኖራቸውም ችግሩ አባብሶታል ብለዋል፡፡

ዶ/ር አሰፋ ለዚሁ ችግር መፍትሄ ይሆናል የሚሉት አንዱ አናሳ ብሔረሰቦች የሚወከሉበት ሆኖ ሁለት የክልል ምክር ቤቶች መቋቋም ሲሆን ከዚሁ በተጨማሪ ህገ መንግሥታቸው ማናቸውም የኢትዮጵያ ዜጎች መብትና ነፃነት በማይጋፋ መልኩ ተደርጎ እንዲሻሻልና ለአገሪቱ ህገመንግሥት ተገዢ እንዲሆን ጠቁመዋል፡፡

በጋምቤላ፣ በቤንሻንጉል ጉምዝ፣ በሐረርና በኦሮሚያ አካባቢ የሚከሰቱ ውጥረቶችና ግጭቶች የህገመንግሥቶች አለመጣጣም በስርዓቱ ወይም በህገመንግሥቱ ችግር የተፈጠሩ ሳይሆን፣ ስርዓቱንና ህገመንግሥቱን በትክክል ባለመተባበሩ በመዛባቱ እንደሆነ ዶ/ር አሰፋ ገልፀዋል፡፡ በኢፌዲሪ ህገመንግሥት አንቀፅ 41 ላይ በግልፅ እንደሰፈረ፣ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በፈለገው የኢኮኖሚ ዓይነት እንቅስቃሴ እንዲያከናውንና በመረጠው በየትኛውም የአገሪቱ ክፍሎች ተዘዋውሮ የመኖርና የመሥራት መብቱ የተጠበቀ ነው፡፡ ህገ መንግሥቱ እነዚህ መሠረታዊና ሰብዓዊ መብቶች ማናቸውም የመንግሥት አካል የማክበርና የመተግበር ግዴታ ይጥልባቸዋል፡፡ ሆኖም አጥኚዎቹ እንደሚሉት፣ አንዳንድ የክልል መንግሥታት ለራስ መስተዳደርና ለራሳቸው ብሔር መብት ብቻ በመቆርቆር የሌሎች አናሳ ዜጎች መሰረታዊ መብቶችን ችላ ማለታቸው ይነቅፋሉ፡፡

እንደ ዶ/ር አሰፋ ምልከታ፣ አዲሱ የፌዴራል ስርዓት የኢትዮጵያ ዜግነታዊ ትስስር እንዲያጠናክር፣ የእርስ በርስ ውጥረት እንዲቀንስ፣ የፌዴራልና የክልሎች ተቋማት የአናሳ ብሔረሰቦች ስጋት ለማስቀረት ምን ያህል እየሰሩ እንደሆነ ይመዝነዋል፡፡

በዚሁ ጉዳይ ላይ ሁለት አስተሳሰቦች ይደመጣሉ፡፡ አንደኛው እነዚህ ችግሮች የስርዓቱ የውስጥ ተቃርኖ እንደሆኑና የብሔረሰብ መቧደንን እያበረታታና የግለሰባዊነት አስተሳሰብ እያጠፋ እንደሆነ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በሌላ በኩል እነዚህና ሌሎች ችግሮች እየታዩ ያሉት ከስርዓቱ አዲስነት፣ ከዴሞክራሲያዊ ሽግግሩ ዝቅተኝነትና የስርዓቱንና የህገመንግሥቱን አተገባበር ጉድለት እንደሆነ ይገለፃል፡፡ እንደ ህንድ፣ ናይጄሪያና ስዊዘርላንድ የመሳሰሉ አገራት ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው ሲሆኑ፣ የሚከተሉት ስርዓትም ይሄው በቋንቋ/በብሔር የተመሰረተው የተሳካ ፌዴራሊዝም ነው፡፡

በመሆኑ "በእነዚህ ችግሮች" ምክንያት ስርዓቱ በኢትዮጵያ አልሰራም ማለት አይቻልም፡፡ አንዳንድ የራሱ ችግሮች ሊኖሩበት የሚችል ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ለዘመናት እየተንከባለለ የመጣው "ብሔራዊ ጭቆና" በማስወገድ ብሔርብሔረሰቦች የራሳቸው ማንነት የመጠቀም ተፈጠሮአዊ መብታቸው አጎናፅፈዋል፡፡ ይሄ አንድ እርምጃ ነው፡፡

ሆኖም በስርዓቱ ዙሪያ ልዩነት ያላቸው ወገኖች "ትምክህተኛ፣ ጎሰኛ" መባባሉ ቀርቶ፣ የጋራ ውይይት ቢያደርጉበትና የአገሪቱ የወደፊት ዕድል በጋር የሚወሰኑበት አጋጣሚ መፈጠር እንዳለበት ባለሙያዎች ያሳስባሉ፡፡ በማከልም ስርዓቱን የሚያጠናክሩ የግጭት አፈታት ዘዴዎችና ተቋማት እንዲዘረጋም ይመክራሉ፡፡ አልፎ አልፎ የሚፈጠሩ ግጭቶች የስርዓቱን መልካም ስም እያጎደፉ በመሆናቸው ተገቢ ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲሰጣቸውም ይጠይቃሉ፡፡
Reporter

No comments: